ባለፈው የፊልጵስዩስ ጥናት የወንጌል መስፋት የደስታው ምክንያት
መሆኑን አይተን ነበር። ይህ ክፍል ከዚያ የደስታ መፍሰስ የቀጠለ ነው።
ቀጣይ ደስታው ከወንጌል ስብከትና ስፋት ያለፈም ነው። አሁን የራሱን
መዳን ፍጹምነት እያሰበም፥ ለነዚህ ሰዎች ያለውን አገልግሎት እያሰበም
ይደሰታል። ክርስትና ደስታ ነው። ወደ ኋላ አይተን ስለመዳናችን፥
ባለንበት ሁኔታም ከጌታ ጋር በመገኘታችን፥ ወደፊትም ወደ አባቱ ደስታ
የምንገባ በመሆናችን እንደሰታለን።
ቁጥር 19፤ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ
ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ ይህ
ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን
በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ
ወትሮው አሁን ደግሞ በሥጋዬ ይከብራል።
ለመዳኔ ሲል አልዳነም ነበር ወይም ደኅንነቱ ገና የተረጋገጠ አልነበረም
ማለት አይደለም። ከእስር ቤት ስለመፈታቱም መናገሩ አይደለም።
ከእስር ስለመፈታት አለመሆኑን ቃሉን ቀጥለን ስናነብብም እንረዳለን።
ስለሞቱ እየተናገረ ስለመፈታት ሊናገር አይችልም። እርግጥ እንደሚፈታ
ተስፋ ያደርጋል፤ (ቁ. 25 እና 2፥24)። እንኳን ያለ ወንጀል የታሰረ የጌታ
እስረኛ ወንጀል የፈጸመውም ለመፈታት ተስፋ ቢያደርግ ማስገረም
የለበትም። ቃሉ ግን σωτηρίαν (ሶቴሪያን) ከክፉ መጠበቅንና ነጻ
መሆንንም ጭምር ቢያመለክትም ዋና አሳቡ ድነት ወይም መዳን ነው።
ቃሉ በክርስቶስ ያገኘነው መዳን የተገለጠበት ዋናው ቃል ነው። ክርስቶስ
መድኃኒት ወይም አዳኝ ሲሰኝም ይኸው ቃል (ሶቴር) ነው የተጻፈው፤
ጳውሎስም ራሱ ይህን ቃል በ3፥20 ጽፎታል። ስለዚህ ሐዋርያው ከእስር
ስለመውጣቱ መዳን መናገሩ አይደለም።
በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 6ን ስናጠና ጌታ ጀማሪም ፈጻሚም አምላክ
መሆኑን አስተውለን ነበር። ይህ የተጀመረ ሥራም የደህንነታችን ጉዳይ
መሆኑን አይተናል። በፊል. 2፥12ም ይህንን መዳንን የመፈጸም ቃል
ይናገራል። ይህ መዳን መጠበቅ፥ መፈጸም፥ መጨረስ፥ ፍጹም መደረግ
ያለበት ነገር ነው። ይህ የጳውሎስ መዳን እንግዲህ የመዳን መቀጠል
ወይም በደኅንነት ውስጥ ሆኖ የመኖር ሁኔታ ነው። በቅድስና የማደግንን፥
በመከራ የመጽናትን፥ የሰማዩን የመናፈቅን፥ ባሉበት ቦታና ሁኔታ ለእርሱ
ክብር መኖርን፥ በዚህም ሁሉ ያ ሰው የዳነ ሰው መሆኑን አመልካች
ነው። ጳውሎስ መታሰሩና በመታሰሩም ምክንያት በገዛ ሕይወቱም ሆነ
በወንጌል መስፋት ምክንያት በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሆኑት
ነገሮች የመዳኑ መገለጫዎች ናቸው።
እነዚህ ነገሮች እንዴት ወይም በምን ኃይል እንደሚሆኑ ሲናገር፥
በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት አለ። መዳናችንን
በፍሬያማነት ቀጣይ ለማድረግ እነዚህ ሁለት እጅግ አስፈላጊ ነገሮች
ናቸው። የቅዱሳን ጸሎት በመንፈሳዊ ጉዞአችንና በአገልግሎታችን
ብርታትና ልቀት ውስጥ ሁነኛ ሚና አለው። የኛም ጸሎት በሌሎቹ
ሕይወት ውስጥ የሚሠራው ድንቅ ሥራ አለው። ሌሎች እንዲጸልዩልን
መጠየቅን፥ እኛም ለሌሎች ቅዱሳን መጸለይን አናቋርጥ።
ሌላው ቃል ἐπιχορηγίας (ኤፒኮሬጊያስ) የሚል ነው። መደገፍንም
መስጠትንም የሚገልጥ ἐπιχορηγέω ከሚል ቃል የመነጨ ነው።
መስጠትን ሲገልጥ፥ መስፈር፥ ማቅረብ፥ መሙላት ማለት ነው።
መደገፍም ማቆም፥ ማበርታት፥ እንዳይንገዳገዱ እንዳይወድቁ መያዝ
ነው። ይህን የሚያደርግ ደግሞ የኢየሱስ መንፈስ ነውና ይህን መንፈስ
ታመነ። የኢየሱስ መንፈስ ከመንፈስ ቅዱስ ስሞች አንዱ ነው።
የፊልጵስዩስን መልእክት መግቢያ ከሐዋ. 16 ስንመለከት በተለይ ቁጥር
6-7 ላይ ይህንን አይተን ነበር። የኢየሱስ መንፈስ የሚለው ቃል በዚያ
እና እዚህም ይገኛል። የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ሰጪው
ኢየሱስ መሆኑን መግለጡ ነው። እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ፥ ለክቶ፥
ቆጥቦ አይሰጥም (ዮሐ. 3፥34)። ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር
ወይም ሙላት ስር ሆኖ መኖር ሁሌም የሚጠበቅበት ኑሮ ነው።
በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የአንድ ቀን ክስተት
ሳይሆን የየእለቱ የራስ ድካም በእርሱ ብርታትና ሁሉን ቻይነት፥ የራስ
አለማወቅ በእርሱ ሁሉን አዋቂነት የሚፈጸምበት ሕይወት ነው።
የመንፈስ ቅዱስ መሰጠትና ሙላት ሕይወት ነው፤ ኑሮ ነው፤ የክርስቶስ
በኛ ውስጥ መኖር፤ የኛም ለክርስቶስ መኖር ነው። የመዳናችን መዳን
እንደሆነ የማለቁ፥ የመፈጸሙ አካሄድ ነው።
ጳውሎስ እነዚህን ሁለት ትልልቅ ነገሮች፥ የቅዱሳንን ምልጃ እና
የክርስቶስን መንፈስ መሰጠት መናፈቁ በመከራውና በእስራቱም ውስጥ
ለክርስቶስ ለመኖርና እስከ ፍጻሜውም ለመጽናት የቆረጠ የቁርጥ ሰው
መሆኑን አመልካች ነው። ይህ ናፍቆቱም ተስፋውም ነው። ይህ ናፍቆቴ
ተስፋዬም ነውና አለ። ናፍቆትና ተስፋ የተለያዩ ግን ተቀራራቢ ነገሮች
ናቸው። ናፍቆት ምኞት ነው፤ ሊፈጸምም ላይፈጸምም ይችላል። ግን
ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። ኤር. ፥ 6
ቁጥር - ኅዳር ፪ሺህ ፬ ዓመተ ezralit@gmail.com ምሕረት NOVEMBER 2011
የውስጣችን መሻት ነው። ተስፋ ግን የሚፈጸምና በተስፋ ሰጪው ላይ
የሚደገፍ ቃል ነው። ተስፋ ሰጪው የታመነ ከሆነ ተስፋው ይፈጸማል፤
ካልሆነ ደግሞ ይቀራል። ጳውሎስ በታሰረበት ወኅኒ ውስጥ ይሁን ወይም
ተፈትቶ፥ በሕይወት ይኑር ወይም ሞቶ ግቡ አንድ ነው፤ እርሱም
የክርስቶስ ክብር። በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት
ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን
ደግሞ በሥጋዬ ይከብራል አለ።
ስለዚህ ለጳውሎስ መኖርም መሞትም ክርስቶስ እስከከበረ ድረስ ትልቅ
ልዩነት የላቸውም። እንዴት ድንቅ ነው! ክርስቲያኖች የምንኖርለት ብቻ
ሳይሆን የምንሞትለትም ምክንያት ያለን ሰዎች ልንሆን ነው የተጠራነው።
ለምንኖርለት ዓላማ ለመሞትም ካልቆረጥን ልንኖርለት አንችልም። ይህ
እውነት ነው። ለምን ቢባል ቁርጠኞች ካልሆንን እምነታችን የተግባር
ሳይሆን የአፍ ብቻ ነው ማለት ነው። ለምንኖርለት ነገር ልንሞት
ከተጠየቅን አንሞትማ! እንሸሻለና! ስለዚህ መኖራችን የለበጣ ነው።
ስለ ሚሊሻ በድሉ ልንገራችሁ። ያኔ የኢትዮ-ሱማሌ ጦርነት ጊዜ አንድ
በድሉ የተባለ ሚሊሻ ወታደር ነበረ አሉ። አንድ ቀን የብርጌዱ አዛዥ
የሆኑት ኮሎኔል፥ “እነዚህን ሽርጣም ሱማሌዎች ማየት እንዳስጠላኝ ያለ
ሌላ የሚያስጠላኝ ነገር የለም። ዛሬ ያንን ኮረብታ ሄደን መያዝና እዚያ
የመሸጉትን ሽርጣሞች ጨርሰን መደምሰስ አለብን፤ እሺ ጎበዝ?” አሉ።
ሁሉም፥ አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት! ሞት! ሁሉም ነገር
ለአብዮቱ! . . . አሉና አንዳንዶቹም ፎከሩና ዘመቻው ተጀመረ። ሚሊሻ
በድሉ አፈግፍጎ ወደ ሰፈር ሲሸሽ ተያዘና ማታ ኮሎኔሉ ዘንድ ቀረበ። ይህ
የወታደሩን ወኔ የሚሰልብ ድርጊት በመሆኑ አዛዡ በቁጣ፥ “እህ ሚሊሻ
በድሉ፥ ለምን ሸሸህ?” አሉት። ሚሊሻ በድሉም፥ “ጌታዬ ኮረኔል፥ እኔም
እንደርስዎ እነዚህን ሽርጣም ሱማሌዎች ማየት እንዳስጠላኝ ያለ ሌላ
የሚያስጠላኝ ነገር የለም፤ ገና ከሩቅ ሳያቸው አስጠሉኝና ጥያቸው ወደ
ሰፈር መጣሁ” አለ።
ሚሊሻ በድሉ ይቅርታ ተደረገለትና ከሠራዊቱ ጋር ቆየ። በሌላ ቀን
ኮሎኔሉ አቅርቦ በሚያሳይ በመነጽራቸው አንድ ጉብታ ላይ አራት ቃኚ
ሱማሌዎች ያያሉ። ከወታደሮቻቸው አራቱን ይመርጣሉ። ሦስቱ ደፋሮች
ናቸው፤ አንዱ ጉብዝናው መፈተሽ ያለበት ሚሊሻ በድሉ ሆነ። ኮሎኔሉ
አራቱን ወደፊት ጠርተው፥ “እዚያ ጉብታ ላይ አራት ሱማሌዎች አሉ፤
እናንተ አራታችሁ ዛሬ አብዮታዊ ወኔያችሁን የምታስመሰክሩበት ቀን
ነው፤ እናንተም አራት፤ እነሱም አራት፤ በሉ ግደሉና መሳሪያቸውን
ይዛችሁ ኑ!” ብለው ሲያሰናብቷቸው አንዱ ወታደር፥ “ኮሮሌር፥ ኢኔ
ሁላት ጋዲሎ ሁላት ማሳራ ዪዞ ዪማላሳል!” አለ። ይኸኔ ሚሊሻ በድሉ፥
“ጎሽ የኔ ጅግና! እንዲያው እናት አንተን ደጋግማ መንታ አድርጋ
ትውለድ! በቃ!” ብሎ አጨበጨበለትና ወደ ኮሎኔሉ ዞሮ፥ “ኮረኔል የኔን
ፋንታ ደበላ ስለሚገልልኝ እኔ ቀርቻለሁ፤ ሁለተኛውን ሽርጣም
የሚገድልበት ሌላ መሳሪያ ከፈለገም ይኸው የኔን ክላሽ እሰጠዋለሁ”
አለ። ሚሊሻ በድሉ በሞት ቀበሌ የሚኖር ሞትን አጥብቆ የሚፈራ ሰው
ነው። ጳውሎስ ከሞት ጋር ሳይፈራ የተጋፈጠ ሰው ነው።
21፤ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።
ለጳውሎስ የኑሮና የአገልግሎቱ፥ የጥሪና የተልእኮው መለኪያ የክርስቶስ
ክብር ነው። ስለዚህ ሞትም ሕይወትም ልዩነት የላቸውም። ለእርሱ
ሕይወት ክርስቶስ ነው፤ የሚኖረው ለክርስቶስ ነው፤ የሚሞተውም
በክርስቶስ ውስጥ ሆኖ ነው። የጳውሎስ ሕይወት የሚያጠነጥንበት አንድ
እንዝርት፥ የሚሽከረከርበት አንድ ዛቢያ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሕይወት
ለእርሱ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ ውጪ ሕይወት የለም። ለጳውሎስ መኖር
ማለት ክርስቶስ ነበረ። ለብዙዎች ምናልባት ሕይወት ዝናና ሥልጣን፥
ክብርና ሞገስ፥ ድሎትና ምቾት፥ አዱኛና ንዋይ፥ ሌሎችም ሊሆኑ
ይችላሉ። ለእኛስ?
ጳውሎስ ሞትንም ጥቅም ነው አለ። ሞትን ጥቅም ነው ማለት የሚችል
በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ጌታ ያወቀ ሰው ብቻ ነው። ሞት
ለክርስቲያን የሚያስፈራ የንግግር ርእስ አይደለም። አንድ ጊዜ ብቻ
የተወለደ ሰው ሁለቴ ይሞታል፤ በሥጋም በዘላለማዊ ሞትም። ዳግም
የተወለደ ሰው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚሞተው። ክርስቲያን ሞትን
የማይፈራው የሞት መውጊያ የተወሰደለት በመሆኑ ነው፤ 1ቆሮ. በሙሉ፥
በተለይም 15፥20 እና 55-56። ጳውሎስ ከታሰረበት ተፈትቶ ቢለቀቅ
ወይም ተጠርቶ ቢገደል ለሁለቱም ዝግጁ ነው። ተርፎ ቢያገለግል ፍሬው
ይበዛል፤ ሞት ተፈርዶበት ከዚህች ምድር ቢሰናበት ወደ ተሻለው ስፍራ
ይሄዳል። በዚያ ስቃይም፥ መከራም፥ እስራትም፥ ግርፋትም፥ በተለይም
ኃጢአትም፥ ሰይጣንም የሉም። ለጳውሎስ ሞት ጥቅም ነበረ። ለእኛስ?
22-26፤ ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ
ኣላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም
ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን
በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ይህንንም ተረድቼ፥
በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ
ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር
ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ።
ይህ ማለት ለመኖር ወይም ለመሞት ጳውሎስ የምርጫ ነጻነት አለው
ማለት አይደለም። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ የሰው ምርጫ
አይደለም። ይልቅስ ጳውሎስ እኛ ልቡን እንድናነብብና እንድናውቅ
ከፍቶ እያሳየን ያለ ነው የሚመስለው። ለማንም አገልጋይ፥ በተለይም
እንደ ጳውሎስ ላለ ራሱን ሳይቆጥብ፥ ለሰውነቱ ሳይሳሳ ለሚያገለግል
ሰው በሕይወት መቆየት በረከት ነው። ጌታ ይከብራል፤ ነፍሳት ይድናሉ፤
ቤተ ክርስቲያንም ትታነጻለች። ለጳውሎስ መሞትም መኖርም ሁለቱም
ትርጉም አላቸው። ሁለቱም እኩል ናቸው። ሁለቱም መፈታት ናቸው።
እንዲያው በሥጋ መፈታትን የሰፋና የነጻነት አገልግሎት አድርገን
ከቆጠርነው እንጂ ታሥሮም እያገለገለ ነው ይህን የጻፈው። ስለዚህ
ሁለቱም ለእርሱ መፈታት ናቸው። ይህ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር
የሚለው መሄድ (ἀναλῦσαι አናሉሳይ) መፈታት፥ መለቀቅ
እንደማለትም ነው። እርግጥም ወደ ጌታ መሄድ መለቀቅ ነው። ወደ ጌታ
መሄድ ልክ ሥጋ ከወኅኒ እንደሚወጣው መፈታት ብቻ ሳይሆን ከዚያም
በላይ መለቀቅ ነው።
ጳውሎስ ቢኖር ለምን እንደሚኖር ጠንቅቆ የተረዳ ሰው ነው። ሞትም
ምን መሆኑን ፈጽሞ ያወቀ ሰው ነው። መኖሩ፥ መፈታቱና ማገልገሉ
ለቅዱሳን በጣም አስፈላጊ ነው። መሞቱም ጥቅሙ ነው። በሁለቱም
ጌታን ማክበርን ሊያከብርበት ሁሌም ስንዱ ሆኖ የኖረ ሰው ነው።
ለሚሞትለት ዓላማ የኖረ፤ ለኖረለት ዓላማም ሊሞት ቆርጦና ዝግጁ ሆኖ
የኖረ አገልጋይ ነው። እኛስ እንዴት ነን? ለምንኖርለት ለመሞት፥